የአማራ ባንክ የ2024/25 በጀት ዓመት፤ የሥራ አፈፃጸም ጉባዔ ከሐምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል፡፡ ጉባዔው ለሦስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፤ የአማራ ባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢና አባላት እንዲሁም ከፍተኛ የባንኩ አመራሮች፣ የዲስትሪክት እና የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች እየተሳተፉበት ይገኛል፡፡
በጉባዔው መክፈቻ፤ የአማራ ባንክ የዳይሬክሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጋሻው ደበበ የበጀት ዓመቱ አፈፃፀምን ለመገምገም ለተገኙት ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የቦርድ ሰብሳቢው እንዳሉት ባንኩ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ገጥመውት ለነበሩት ተግዳሮቶች አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እንደተደረገና ዶ/ር ዮሐንስ አያሌውን የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመሆን ከሾመበት ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለውጡን የመሩበት መንገድ የሚያስደንቅ እና በበጀት ዓመቱ ለተመዘገበው ውጤት መሠረት የሆነ ነበር፡፡
ቦርዱ በተገባደደው በጀት ዓመት የባንኩን ለውጥ እና የወደፊት ዕድገትን ለመደገፍ ያስችል ዘንድ በርካታ ቁልፍ የሚባሉ ውሳኔዎችን እንዳስተላለፈ በተለይም ለረጅም ጊዜ ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በማሻሻል ረገድ በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሾሙ ቦርዱ ለባንኩ ሁለንተናዊ ዕድገት የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሳይ የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው በበኩላቸው ባንኩ በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ገጥሞት የነበረውን ተግዳሮት ለመፍታት የባንኩ የዲይሬክተሮች ቦርድ ማስተዋል የተሞላበት ብልህ እርምጃ በመውሰድ በአዲስ መልክ እንዲደራጅ አድርጎ ወደ ሥራ በማስገባቱ ባንኩ ወደ ስኬት በከፍተኛ እርምጃ መጓዝ እንዲጀምር አስችሎታል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ዮሐንስ በሪፖርታቸው ይፋ እንዳደረጉት የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ብር 31.5 ቢሊዮን ማድረስ መቻሉ እና የደንበኞቹን ቁጥር ከ2.4 ሚሊዮን በላይ እንዲሁም የቅርንጫፎቹን ቁጥር 316 ማድረስ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ባንኩ በቅርቡ ባስተዋወቀው ለወዳጄ የዲጂታል አነስተኛ ብድር አገልግሎቱ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ ከ97 ሺህ በላይ ለሆኑ ደንበኞች ብድር ያቀረበ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥም ሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና በአነስተኛ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ዋነኞቹ ተጠቃሚዎች እንደነበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ አማራ ባንክ 70.8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጪ ምንዛሬ ማግኘት እንደቻለ ገልጸዋል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል 8.6 ቢሊዮን ብር ማድረስ እንደተቻለም አስታውቀዋል፡፡
በብድር አሰባሰብ ረገድ በዓመቱ 10.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፣ ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ236.3 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
አማራ ባንክ በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙና በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፍ ለተሰማሩ ደንበኞቹ የሰጠው ጠቅላላ የብድር መጠን ከብር 26 ቢሊዮን በላይ ማድረሱንና የተበላሸ የብድር መጠኑ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው ከፍተኛ ጣራ በታች መሆኑን የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡
ይህ ውጤት የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ፣ የማኔጅመንት አባላትና ሁሉም የባንኩ ሠራተኞች በጋራ ባደረጉት ጥረት የተመዘገበ መሆኑን እውቅና በመስጠት፣ ሁሉም በየደረጃው ላበረከተው አስተዋጽዖ አመስግነው፤ አዲሱን የበጀት ዓመት በአዲስ ስትራቴጂ፣ ደንበኛ ተኮርና ቀልጣፋ አገልግሎት ስኬታማ ሆነን እንደምናጠናቅቅ ተስፋ አደርጋለሁ በማለት፤ ደንበኞችም አማራ ባንክ በያዘው የለውጥ አቅጣጫ ፍላጎታቸውን ያማከለ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን አውቀው ከአማራ ባንክ ጋር አብረው እንዲሰሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡