አማራ ባንክ የ2024/25 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማና የ2025/26 በጀት ዓመታዊ የዕቅድ ውይይት የሥራ አመራሮች ጉባዔ ሐምሌ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ሲያጠናቅቅ፣ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዲስትሪክቶች፣ የዋና መሥሪያ ቤት የሥራ ክፍሎች፣ ቅርንጫፎችና በግል የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሰራተኞች ዕውቅና እና ሽልማት አበርክቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ ባንኩ ላስመዘገበው ውጤትና የባንኩን የ5 ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በመገምገም፤ በማጽደቅና የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማደረግ ባንኩ ከገባበት ጫና በማላቀቅ ሂደት የበኩላቸውን አመራር ሲሰጡ ለነበሩ የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ አባላት ላደረጉት አስተዋፅዖ የባንኩን ሰራተኞች በመወከል የባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ምስጋና አቅርበዋል፤ ዕውቅናም ሰጥተዋል፡፡
የባንኩ ሰራተኞች በዋና ሥራ አስፈፃሚው ለተደረገው አመራርና ሪፎርም ያዘጋጀውን ልዩ ምስጋናና ሽልማት በባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጋሻው ደበበ አማካኝነት ለባንኩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው አበርክቷል፡፡
በጉባዔው ማጠናቀቂያ ባለፈው በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ዲስትሪክቶች፣ የሥራ ክፍሎች፣ ቅርንጫፎች እና ግለሰቦችን ለማመስገን የዋንጫ፣ የምስክር ወረቀት እና የገንዘብ ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ባንኩ ለዲስትሪክቶች፣ ለዋና መሥሪያ ቤት የሥራ ክፍሎች፣ ለቅርንጫፎችና በግል የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሰራተኞች ዕውቅና እና ሽልማት ያበረከተው በተለይ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣በብድር አሰባሰብ፣ የደንበኞች አገልግሎት፣ዲጅታል ባንኪንግ፣ ባንኩ በቀጣይ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማበልፀግ እና ሌሎች የአፈፃፀም መለኪያዎች ለሽልማት የተቀመጡ መስፈርቶች ነበሩ፡፡
የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ለተሸላሚዎች እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንዳሉት ይህ አይነቱ የእውቅናና የሽልማት መርሃ ግብር በቀጣይ ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ ባንኩ ያስቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካት መረባረብና ለላቀ ሥራ በመነሳሳት እንዲሰሩ ጠይቀው፣ በቀጣይ ሁሉም ለሽልማት እጩ መሆን ይገባዋል።
የአማራ ባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጋሻው ደበበ በበኩላቸው፤ በአዲሱ በጀት ዓመት ከዚህ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ እና በዕቅዱ የተቀመጡ መለኪያዎችን ለማሳካት ሁሉም የባንኩ ሰራተኞች በጋራና በብርታት እንዲሰራና የባንኩን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ለማሳካት እንዲጥሩ ከአደራ ጋር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ባንኩ እንዲህ አይነት የእውቅናና የሽልማት መርሃ ግብር ማዘጋጀቱ፣ የላቀ የአፈፃፀም ደረጃን መቀበልና እውቅና ለመስጠት፡ ልዩ አፈፃፀም፣ ትጋት እና ፈጠራ ላሳዩ ሰራተኞች እና የሥራ ክፍሎች እውቅና ለመስጠት እና ለማክበር፣ሌሎች ሰራተኞችና አመራሮች ለአማራ ባንክ ስኬትና ለላቀ ሥራ ለማነሳሳት፣ ለባንኩ ስኬት አስፈላጊ የሆኑትን እሴቶች እና መልካም ባህሪያት ለማጠናከር፣ ባንኩ ያስቀመጣቸውን ግቦች ማሳካት የሚያስችል መነሳሳት ለመፍጠር፣ በሰራተኛው መካከል ተባብሮ ለመሥራት ባህል ለመገንባት፣ የባለቤትነት ስሜትን የሚያጎለብት አዎንታዊ እና አመስጋኝ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር፣ ምስጋናን ለመግለጽና በባንኩ ውስጥ የላቀ አስተዋፅዖ ላበረከቱት ያለውን ልባዊ ምስጋና ለማሳየት እንደሆነም በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።