አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፣ ነሐሴ 06 ቀን 2017 ዓ.ም አማራ ባንክ ከልደታ ክፍለ ከተማ ጋር በመተባበር በክፍለ ከተማው ስር የሚገኙ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ ለመኖሪያ ምቹ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታወቀ።
ባንኩ በክረምቱ ዝናብ ምክንያት ለመኖር እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ቤቶችን ከወረዳውና ከክፍለ ከተማው አስተዳደር ጋር ሆኖ በቅርበት ከለየ በኋላ እስከ ዘመን መለወጫ ባሉት ቀናት ሰርቶ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራና የተቸገሩ አቅመ ደካማ ቤተሰቦች ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ለማድረግ መታቀዱን በማስጀመሪያ መርሃ ግብር ወቅት ተገልጿል።
ባንኩ ገንብቶ ለአቅመ ደካሞች የሚያስረክባቸው ቤቶች ከባንክ አገልግሎት ባሻገር በህብረተሰቡ ዘላቂ ኑሮ መሻሻል ላይ መዋዕለ-ንዋይ በማፍሰስ ከባንክ ባሻገር የሚለውን መሪ ሃሳብ በተግባር የሚያሳይበት እንደሆነ ነው የአማራ ባንክ የዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወካይ የሆኑት አቶ እሸቴ የማታ በማስጀመሪያ መርሃ ግብር ወቅት ያስታወቁት።
እኛ ከባንክ ባሻገር እንደሆንን እናምናለን ያሉት ተወካዩ፤ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ ቤቶችን መገንባት ጠንካራ እና የበለጸገ ማህበረሰብ ለመፍጠር መሰረታዊ ነገር በመሆኑ፣ እንደ አማራ ባንክ ይህ አይነቱ የማህበራዊ ኃላፊነት የመወጣት ተግባር ማህበረሰባችንን ከፍ ለማድረግ እና ለሁሉም ብሩህ የወደፊት ተስፋ ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።
የቤት እድሳት ስራው በአጭር ጊዜያት ውስጥ ተገንብቶ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የአማራ ባንክ በልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ በተረከበው ቦታ የዋና መስሪያ ቤት ግንባታውን ለማስጀመር በዝግጅት ነው። ባንኩ አሁን በክፍለ ከተማው ተገኝቶ ያደረገው ድጋፍም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅርበት ችግሮችን እየፈታ ለመስራት ያለውን አቋም ማሳያ መሆኑን ነው በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ወቅት የክፍለ ከተማው የዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወካይና የበጎ ፈቃድና የህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ እንግዳው ጓዴ የገለጹት።
የአማራ ባንክ ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት ባሻገር ተደራሽነቱን በማስፋት ለማህበረሰብ ልማት ቁርጠኛ ሆኖ በመስራት ላይ ነው። በማህበራዊ ኃላፊነት ተግባራት፣ ባንኩ ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በንቃት በመደገፍና ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲያጋጥሙ አጋርነቱን ማሳየት፣ ለህብረሰተቡ ፋይዳ ያላቸው የአጭርና የረጅም ጊዜ ልማትን በሚያበረታቱ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ለህብረተሰቡ ያለውን ድጋፍ የሚያረጋግጥ ሲሆን፤ ይህንን ድጋፍ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎችም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
አማራ ባንክ
ከባንክ ባሻገር!