ኤኢትሬድ ግሩፕ እና አማራ ባንክ በአጋርነት በመስራት የኢትዮጵያ ወጣቶችን ለማብቃት እና የዲጂታል የንግድ ልውውጥ በሶኮኩ አፍሪካ በኩል ለመፈፀም የሚያስችላቸውን ስራዎች በመስራት ላይ መሆናቸውን አስታወቁ።
ከሰሞኑ የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ንግድ ግሩፕ እና የአማራ ባንክ በኢትዮጵያ ዲጂታል እና የፋይናንስ አካታችነትን በሶኮኩ አፍሪካ ፕላትፎርም አማካኝነት ለማፋጠን ያቀደ አዲስ ጅምር በቅርቡ ይፋ አድርገዋል። በተለይ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ከኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ከ400 በላይ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የዲጂታል ንግድ አመቻች ሆነው እንዲያገለግሉ ለማድረግ የሚያስችል ስልጠና መስጠት ጀምረዋል።
የኤኢትሬድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉዓለም ሥዩም በዚህ ወቅት እንዳሉት ከ400 በላይ ወጣት ኢትዮጵያውያን የዲጂታል ንግድ አስተባባሪ ሆነው እንዲያገለግሉ ከሰሞኑ ስልጠናውን መስጠት መጀመራቸውን አስታውቀዋል። ይህ ፕሮግራም የክህሎት ማጎልበት ብቻ ሳይሆን ኑሮን ለማሻሻል፣ የስራ እድሎችን ለማስፋት እና ኢትዮጵያን በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስር እየተገነባ ባለው አዲስ አህጉራዊ ኢኮኖሚ ውስጥ ተሳታፊ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ጠቀሜታ በተለይ ኢትዮጵያ የቀጠናውን ነፃ ንግድ ያፀደቀች በመሆኑ ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታውን በማሳየት “በኢትዮጵያ የተመረቱ” ምርቶችን በመላው አፍሪካ በነፃነት እንዲገበያዩ የኤኢትሬድ ግሩፕ በሮችን ለመክፈት እንደሚያስችል የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ይህም ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ውስን የውጭ ምንዛሪ ጥገኝነት በመቀነስ ተጨማሪ እሴትን ጨምረው የተመረቱ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ አዳዲስ መንገዶችን ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው አቶ ሙሉዓለም የገለፁት።
የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ንግድ ግሩፕ በአፍሪካ ህብረት እና በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ሴክሬታሪያት በአህጉሪቱ ውስጥ የዲጂታል እና የፋይናንስ አካታችነትን ለማበረታታት የተመሰረተ ድርጅት መሆኑን የገለፁት አቶ ሙሉ ዓለም ሥዩም ከአማራ ባንክ ጋር ያለው የስራ ግንኙነትም የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለስራ የሚያስፈልጋቸውን ፋይናንስ በማቅረብና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ምርታቸውን በሶኮኩ ፕላትፎርም አማካኝነት ለገበያ እንዲቀርቡ ማስቻል እንደሆነ እና ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት መሆኑንም አስታውቀዋል።
የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው፣ በዚህ መርሃ ግብር ላይ ለተገኙ ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር ‹‹ይህ ትብብር ለሀገራችን ኢኮኖሚ ትልቅ ፋይዳ ያለው ሲሆን፣ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ማብቃት የባንካችን ተልዕኮ ነው››። ‹‹እንደ አማራ ባንክ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እና በፈጠራ የታገዘ የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት በገባነው ቁርጠኝነት በፅናት እንቀጥላለን›› ብለዋል።
በስልጠናው ወቅት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው የሶኮኩ አፍሪካ ፕላትፎርም በርካታ ጠቀሜታዎች እንደሚያመጣ ጠቅሰው በተለይ፡-የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ዕድገት በማጎልበት ለማኅበረሰቡ የሥራ ዕድልን የሚፈጥር፤ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈጣሪዎች ትልቅ እንቅፋት ሆኖ የቆየውን የፋይናንስ ችግር የሚቀርፍ እና ተመጣጣኝ ፋይናንስ እንዲያገኙ የሚያስችል፤የሶኮኩ አፍሪካ የንግድ ሥራዎችን አስፈላጊ ከሆኑ የፋይናንስ አገልግሎቶች ጋር የሚያገናኝ፣ እንቅፋቶችን በመቅረፍ ሥራቸውን እንዲያሳድጉ የሚያግዝ፤የዲጂታል ግብይቶችን እና ፋይናንስን በማመቻቸት ዘርፉ ዘመናዊ የፋይናንስ አካታችነትን እና የንግድ እንቅስቃሴው በዘመናዊ መርህ ውስጥ እንዲያልፍ የሚያግዝ መሆኑን በመረዳቱ ነው ባንኩ አብሮ መስራት የወሰነው ብለዋል።
የሥራ እና ክህሎት ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው ወጣቶች በኤኢትሬድ አፍሪካ ግሩፕና በአማራ ባንክ አማካኘነት የዲጂታል እና የፋይናንስ አካታችነትን በሶኮኩ አፍሪካ አማካኝነት በኢትዮጵያ እንዲፋጠን እና የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችን ተሳትፎ በሀገሪቱ በላቀ ደረጃ እንዲያድግ ድልድይ የሚሆኑ ሰልጣኞች የቀረበላቸውን እድል በአግባቡ እንዲጠቀሙ እና በትኩረት በመስራት ለውጥ እንዲያመጡ አሳስበዋል።
አማራ ባንክ እና የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ በጋራ በመሆን የኢትዮጵያን የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች (SMEs) ምርታቸውን እንዲሸጡና እንዲያስተዋውቁ የሚያስችል ስራዎችን ለመስራት በሂደት ላይ ይገኛሉ። ይህ ትብብር በኤ.ኢ.ትሬድ የፈጠራ ውጤት የሆነው ‹‹ሶኮኩ አፍሪካ›› የዲጂታል ፕላትፎርም አማካኝነት የሚከናወን ሲሆን፣ ከ200,000 በላይ ኢንተርፕራይዞችን በማሰልጠን፣ ወደ ምርት እንዲገቡና ከፍተኛ የገበያ ዕድል እንዲያገኙ ማገዝ እና የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ያለመ ነው።
አማራ ባንክ
ከባንክ ባሻገር!