የአማራ ባንክ ጠቅላላ ሀብት 43 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀ የ23.2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የአማራ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዮሐንስ አያሌው (ፒኤችዲ) አስታወቁ።
የአማራ ባንክ የባለአክስዮኖች 4ኛ ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሚሊኒየም አዳራሽ ከሰሞኑ ተካሂዷል።
በጠቅላላ ጉባኤው ባለአክሲዮኖች፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የማኔጅመንት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤትና የሚዲያ ተወካዮች በተገኙበት የባንኩ ዓመታዊ አፈጻጸምና ሌሎች የፋይናንስና ፋይናንስ ነክ ባልሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ የተካሄደ ሲሆን፣ በዚህ ወሳኝ ጉባኤ የባንኩ የቀጣይ ዓመታት ጉዞ ውይይት ተደርጎበታል።
የዓለም ዓቀፍ የኢኮኖሚ መዋዠቅና በአገር ውስጥ በመንግስት በተካሄደው መዋቅራዊ ማስተካከያ በታየበት ዓመት አማራ ባንክ ልዩ ጥንካሬና ተወዳዳሪነት በማሳየቱ በ2017 በጀት ዓመት አመርቂ የፋይናንስ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ ተገልጿል።
በጉባኤው የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮሐንስ አያሌው (ፒኤችዲ) እንዳሉት፣ ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 655 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ85 በመቶ ብልጫ ያለው ነው።
የባንኩ የብድር ክምችት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ29 በመቶ በማሳደግ ወደ 25.5 ቢሊዮን ብር ማሳደግ የተቻለ ሲሆን፣ ይህም ባንኩ የቢዝነስ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ የሚያደርገው ጥረት እያደገ መምጣቱ እንደሆነ ተመላክቷል።
አማራ ባንክ በ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ26 በመቶ በማሳደግ ወደ 31.5 ቢሊዮን ብር አሳድጓል። ይህም ደንበኞቻችን በባንካችን ላይ እያሳደሩት ያለው እምነት እያደገ መምጣቱ እንደሚያሳይ ተገልጿል።
የባንኩ አጠቃላይ ገቢ በ29 በመቶ በማሳደግ ወደ 5.6 ቢሊዮን ብር መጨመር መቻሉንም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው ለጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች ይፋ ያደረጉት።
ሌላው አማራ ባንክ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት አመርቂ ውጤት ያስመዘገበው በዲጂታል ባንክ ሽግግር ለማድረግ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሰራ ሲሆን፣ ይህም ተደራሽነትን በማስፋት አገልግለቱን የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ነው።
የባንኩ ደንበኞችን ቁጥር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ 2.4 ሚሊዮን በማሳደግ ላይ መሆኑ በአገልግሎቱ መተማመን እና እርካታ እያደገ መምጣቱም ተመላክቷል።
የሴቶችንና በአነስተኛ የንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ አቅም ለማጎልበትም የዲጂታል ማይክሮ ብድር አገልግሎት 1.8 ቢሊዮን ብር ለ95,796 ደንበኞች መስጠት መቻሉን እና በዚህ ዘርፍ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሳደግ እንደሚሰራም ተገልጿል።
ባንኩ እነዚህን ስኬቶች ሊያስመዘግብ የቻለው ባለፈው ዓመት የነበሩበትን ውስብስብ የሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችና ብልሹ አሰራሮች በተለይ፣ የደንበኞች የገንዘብ ክፍያ መስተጓጎልን በማስተካከሉ፣ያልተከፈለና እየጨመረ የሚሄድ የውጭ ምንዛሬ ዕዳ መፍትሄ መስጠት በመቻሉ፣ በከፍተኛ ደረጃ የተበላሸ የብድር ክምችት ለመቀነስ በትጋት በመስራቱ፣ ያስመዘግብ ከነበረው ከፍተኛ ኪሳራ ወጥቶ ወደ ትርፍ እንዲመጣ በመስራቱ፣ በርካታ ከባንኩ ብድር የወሰዱ ፕሮጀክቶች በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ያቆሙትን ሥራ እንዲቀጥሉ በማስቻሉ፣ ወደ ሌሎች ባንኮች የሄዱ በወጪ ንግድና በተለያዩ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ የባንኩ ደንበኞችን ለመመለስ በትኩረት መስራት መቻሉና ያጋጠመውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እጥረት መፍታቱ ባንኩ ላስመዘገበው ውጤት መሻሻል ምክንያት እንደሆነም ነው በጠቅላላ ጉባኤው መክፈቻ ወቅት የተገለፀው።


