አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፣ ታህሳስ 03 ቀን 2018 ዓ.ም የአማራ ባንክ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ብቻ (ከሐምሌ 1 እስከ ህዳር 30 ቀን 2018) በዋና ዋና የፋይናንስ አፈጻጸም ቁልፍ የሥራ መስኮች ላይ ጠንካራና ከፍተኛ ዕድገት በማስመዝገብ ከታክስ በፊት የ1.15 ቢሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል።
ይህ የላቀ ትርፍ የተገኘው በ2017 በጀት ዓመት ከተመዘገበው የ910.2 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል። በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አምስት ወራት 3.55 ቢሊዮን ብር ገቢ ማስመዝገብ እንደተቻለ ዋና ስራ አስፈፃመሚው ጠቅሰዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለውም በእነዚህ አምስት ወራት ውስጥ የተመዘገበው አፈጻጸም ስትራቴጂካዊ ትኩረት በጠንካራ የሀብት ማሰባሰብ፣ በዲጅታል ትራንስፎርሜሽንና በብድር አስተዳደር ላይ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ላይ አተኩሮ መስራት በመቻላቸው የመጣ ነው ብለዋል።
ቁልፍ የአፈጻጸም ዋና ዋና መረጃዎች፡-
የተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ፡
አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን እስከ ህዳር 2018 ዓ.ም 35.8 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ዕድገቱ 82 በመቶ ሆኗል። ይህም በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ የ4.29 ቢሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል።
የውጭ ምንዛሪ (FCY) አሰባሰብ፡-
የአማራ ባንክ የ76.58 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ በመሰብሰብ የላቀ አፈጻጸም አሳይቷል፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ313 በመቶ ብልጫ አለው።
የብድር አቅርቦትና የሀብት ጥራት፡-
አማራ ባንክ ከተመሰረተ ጀምሮ ያቀረበው አጠቃላይ ብድርና የቅድሚያ ክፍያ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት በ53.8 በመቶ በማሳደግ ወደ 31.3 ቢሊዮን ብር አበድሯል።
በብድር አሰባሰብ፡-
በህዳር 2017 ከነበረበት 12.9 በመቶ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ያልተከፈለ/የተበላሸ/ ብድር (NPL) ጥምርታ በአስደናቂ ሁኔታ በማውረድ ወደ 4.06 በመቶ እንዲደርስ ርብርብ ተደርጓል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ኅዳር 20 ቀን 2018 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው በባንኩ 4ኛ ዓመታዊ የባለአክሲዮኖች ጉባኤ ላይ በከፍተኛ ጉጉት የተሰባሰበው ተሳታፊ ከጠዋቱ ጀምሮ ሲታይ አስደሳች ድባብ ፈጥሮ የነበረ ሲሆን በአስደናቂው ቀን ከጠዋቱ 3፡30 ላይ ዝቅተኛው የምልአተ ጉባኤ ገደብ መሟላት ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ መሻገር ችሎ ነበር። ይህም ባለአክሲዮኖች በአማራ ባንክ ራዕይ እና አመራር ላይ ያላቸውን ጥልቅ እምነትና ቁርጠኝነት ያሳያል። ለዚህምልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
አማራ ባንክ
ከባንክ ባሻገር!


