ባንኩ በ2018 በጀት ዓመት በስምንት ወራት ውስጥ 1.82 ቢሊዮን ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን፣ አጠቃላይ ሀብቱም 52.76 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል።
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ — መጋቢት 03 ቀን 2018 ዓ.ም
የአማራ ባንክ ባለአክሲዮኖቹ፣ ደንበኞቹ፣ ተቆጣጣሪ ተቋማትና በአጠቃላይ ለመላው ህብረተሰብ ባንኩ በፋይናንስ የተረጋጋ፣ ጤናማ አሰራር የዘረጋ፣ የብሄራዊ ባንክ ያወጣቸውን የቁጥጥር መመሪያዎችን በጥብቅ የሚከተልና የሚያከብር መሆኑን ያረጋግጣል። ባንኩ የቀን ከቀን ሥራውን የባንክ ቢዝነስ አሰራር መርሆዎችንና መመሪያዎችን በመከተል እያከናወነ ነው።
በቅርቡ በአንዳንድ ሚዲያዎች የተሰራጩ ዘገባዎች የባንኩን የአሁናዊ ሁኔታ ያላሳዩ፣ የመደበኛ አገልግሎትና የፋይናንስ አሰራር ሁኔታን በአግባቡ ያልተገነዘቡ፣ አብረውን የሚሰሩ ደንበኞቻችንን የማይመጥኑና የተሳሳቱ መረጃዎችን ለህዝብ ያቀረቡ ሆነዉ ተገኝተዋል፡፡
አማራ ባንክ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የባንኩን አሁናዊ እውነታዎች፣ ባንኩ ያሳየውን ቀጣይነት ያለዉ እድገት፣ የገነባዉን ጠንካራ የአስተዳደር ስርዓትና በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ዙሪያ ግልፀኝነት ያለው አሰራር በማስፈን ረገድ ያለዉን ቁርጠኛ አቋምና ተግባር ለማሳወቅ ይህን መግለጫ አዉጥቷል።
ጠንካራ የፋይናንስ አቅምና የሀብት ጥራት
- አማራ ባንክ የብድር ፖርትፎሊዮና የክሬዲት ተጋላጭነቱን አስመልክቶ ሙሉ በሙሉ በብሔራዊ ባንክ በተላለፉ የጥንቃቄ መመሪያዎች ገደብ ውስጥ ሆኖ በመፈፀም ላይ ነው።
- የአማራ ባንክ ለአንድ ተበዳሪ የሚሰጠው ጠቅላላ የብድር መጠን ብሄራዊ ባንክ ከፈቀደው የቁጥጥር ገደብ የ25 በመቶ በታች ሲሆን፣ ይህም የብሄራዊ ባንክን የአደጋ ስጋት መመሪያዎችን በጥብቅ በመከተል የተፈጸመ ነዉ፡፡ ወደ ባንካችን መጥተው አሁን ላይ ብድር ከወሰዱ የግለሰብ ደንበኞች ከ25 በመቶ በላይ ባንኩ ብድር አላቀረበም።
- እ.ኤ.አ የ2025/26 በጀት ዓመት የስምንት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት መሰረት ባንኩ የሀብት ጥራቱን ለማጠናከርና ለማሳደግ እየሰራ ሲሆን፣ የተበላሸ ብድር ምጣኔ (NPL) መጠንን ወደ 4.9 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም በፋይናንስ ኢንዱስትሪውና በብሄራዊ ባንክ ተቀባይነት ያለዉ መጠን ዉስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነዉ፡፡
- ባንኩ የብድር ክትትል፣ የአመላለስና የማገገም ስርዓቶች በመዘርጋቱ የፖርትፎሊዮ አፈፃፀሙ በከፍተኛ መጠን እንዲጠናከርና እንዲሻሻል አድርጓል። በዚህም ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ ከ9.9 ቢሊዮን ብር በላይ ከብድር መሰብሰብ ችሏል።
- ባንካችን ውስጥ የአደጋ ስጋት አስተዳደርና የውስጥ ቁጥጥር ስርዓቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተጠናከሩ ነው። ይህም ዘላቂነት ያለው የብድር አቅርቦት እንዲኖር በማገዝ ላይ ነው።
- ባንካችን በአሁኑ ሰዓት የተለየ የጥሬ ገንዘብ እጥረት የሌለበት ሲሆን፣ ይህን ችግር ከፈታ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በሞባይል ባንኪንግ አማካኝነት እስከ 1 ሚሊዮን ብር ድረስ ማስተላለፍ እንዲችሉ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ ይህን በማድረግም አማራ ባንክ በተሻለ እርቀት መጓዝም ችሏል፣
- ሌላው በዲጂታል አነስተኛ ብድር በርካቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ በፋይናንስ አካታችነት ጉልህ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። በዚህም ባንኩ ከ 5.1 ቢሊዮን ብር በላይ በዲጂታል አነስተኛ ብድር የሰጠ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 90 በመቶው ለሴት ተበዳሪዎች የቀረበ ነው። በአጠቃላይ በዲጂታል አነስተኛ ብድር ከ240 ሺህ በላይ ደንበኞች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
- ይህ ሁሉ ጥረት ባንኩ ጥንቃቄ ያለው የፋይናንስ አስተዳደርና ኃላፊነት ያለው የብድር ስርዓት እንዳለው ያሳያል።
የስትራቴጂ ለውጥ ስለመደረጉና የባንኩ ዕድገት
ባንኩ በአሁኑ ወቅት የአምስት ዓመት የስትራቴጂያዊ ዕቅዱን በተግባር እያስፈጸመ ሲሆን፣ ይህም የስራ ብቃትን ለማሳደግ፣ የሚሰጣቸውን የፋይናንስ አገልግሎቶች ለማስፋፋትና የረጅም ጊዜ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ሂደት ለማስቀጠል እየሰራ ነው።
የዚህ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አካል ከሆኑትና ባንኩ ከወሰዳቸው አስፈላጊ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መካከል፦
- አዲስ መዋቅር በማስጠናትና በመተግበር ጀምሯል፡፡ እ.ኤ.አ ከማርች 1/2026 ጀምሮ አዲስ የደመወዝ ስኬል ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
- የተቀማጭ ገንዘብ እድገትን ለማፋጠን የሀብት ማሰባሰብ እንቅስቃሴዎችን በማስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡
- የባንኩን የአገልግሎት አሰጣጥና የውስጥ ክትትል ስርአቶች ለማጠናከርና ለማዘመን በመስራት ላይ መሆኑም ይታወቃል።
የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት
- አማራ ባንክ በተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ዘርፍ የሚያበረታታ ዕድገት እያሳየ ነው። የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ እስከ ፌብሩዋሪ 28 ቀን 2026 ድረስ ባሉት ቀናት 37.9 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉ፣ ይህም ባንኩ ላይ ህዝቡ ያለው እምነት እየጠነከረና እያደገ መምጣቱን ያሳያል።
- ባንኩ የ2024/25 አፈጻጸምን መሰረት በማረግ ለባለአክሲዮኖቹ የትርፍ ክፍፍል (Dividend) ፈፅሟል። ይህም የባንኩ የፋይናንስ አፈፃፀም እየተሻሻለ መሆኑንና ለባለአክሲዮኖቹ እሴት ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
- እ.ኤ.አ ከጁን 2022 ስራውን ከጀመረ ወዲህ ባንኩ አገልግሎቱን በማስፋፋት፣ የአስተዳደር ስርዓቶችን በማጠናከርና ዘላቂ የፋይናንስ መሠረት በመገንባት ጉልህ እድገት አሳይቷል።
ግልጽነትና ኃላፊነት ያለው አገልግሎት ስለመስጠቱ፣
አማራ ባንክ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ግልጽነትንና ኃላፊነትን ለማጠናከር ሚዲያ ያለውን ሚና ይገነዘባል። ሆኖም ግን በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚወጡ ዘገባዎች በተረጋገጡ እውነታዎች፣ በተቆጣጣሪ ተቋማት ግኝቶችና በሚዛናዊ አቀራረብ መመስረትና መዘገብ አለባቸው። በመሆኑም አማራ ባንክ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቋሙን የስራ አፈፃፀም ለይፋዊ ኮምዩኒኬሽን በመጠቀምና ለህዝብ ከመድረሳቸው በፊት ኦዲት የተደረጉ የፋይናንስ ሪፖርቶችን መጠቀም፣ የብሄራዊ ባንክ የሚያወጣቸውን የቁጥጥር መግለጫዎችንና መመሪያዎችን በመጠቀም መረጃዎችን ለህዝብ እንዲያደርሱ ማድረግ ያስፈልጋል።
አማራ ባንክ አሁናዊ ቁመናው በፋይናንስ የተረጋጋ፣ ጤናማ አሰራር የዘረጋና በረጅም ጊዜ እድገት ላይ አተኩሮ እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን እናረጋግጣለን። ባንኩ ራሱን ለማጠናከርና ለኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ እድገት ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ ለማበርከት ከተቆጣጣሪዎች፣ ባለአክሲዮኖችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት መስራቱን ይቀጥላል።
የዳይሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንቱ በጋራ የባለአክሲዮኖችን ሀብት መጠበቅ፣የተቀማጭ ገንዘብ ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የህግና የቁጥጥር መመሪያዎችን መከተል፣ የተቋማዊ አስተዳደርን ማጠናከርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማት የበኩሉን ድጋፍ መስጠት ተግባራትን በመፈፀም ግልጸኝነትና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የባንኩን ቀጣይነት ያለዉ እድገት ለማስቀጠል የማይናወጥ ቁርጠኝነታቸውን ያረጋግጣሉ።
ደንበኞቻችን፣ ባለአክሲዮኖቻችን፣ ሰራተኞቻችን፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክና ባለድርሻ አካላት ለአማራ ባንክ ስለሚያሳዩት ቀጣይነት ያለው እምነትና ድጋፍ ምስጋና ያቀርባል።
የአማራ ባንክ ይህን ፕሬስ ሪሊዝ ያዘጋጀው የባንካችንን አሁናዊ ሁኔታ ባለአክሲዮኖቹ፣ ደንበኞቹና ህብረተሰቡ በአግባቡ እንዲረዱት ለማድረግና በተመሳሳይ በባንኩ ላይ የተከፈተው የሚዲያ ዘመቻ ሆን ተብሎ በባንኩ ላይ ጫና ለማሳደርና መደበኛ የባንክ አገልግሎቱን በአግባቡ እንዳይሰጥ ለማወክ እንደሆነ ለማሳወቅ ነዉ፡፡
ሪፖርተር የአማራ ባንክን አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ ውስጥ ያካተታቸው መረጃዎች በተለይ ህዝቡን ለማሳሳት የቀረቡ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉን ማናቸዉንም የባንኩን የስራ ኃላፊዎች አስተያየት ያላካተተ፣ በአብዛኛው በስም ያልተጠቀሱ ምንጮችን የተጠቀመ፣ ሀሰተኛና ባልተረጋገጡ መረጃዎች እና ሆን ተብለው የባንኩን ስም ለማበላሸት በማሰብ ለራስ ፍላጎትና ዓላማ በተመረጡ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ዘገባን ለህዝብ ማጋራቱ ተገቢነት ያለዉ ሆኖ አላገኘነዉም፡፡
ጋዜጣዉ እንደ ባንክ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍቷል፤ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ለህትመት አብቅቷል። እንደ አንድ በቅርብ ዘርፉን እንደተቀላቀለ ባንክ ቀላል የማይባል ጉዳት አድርሷል።
ባንኮች በደንበኞች፣ በአክሲዮን ባለቤቶች እና በህዝብ እምነት ላይ የተመሰረቱ ስለሆኑ እንዲህ ዓይነት ሀሰተኛ ዘገባ ያልተፈለገ ግርግርና መረበሽን ሊፈጥር ይችላል።
ይሁንና አማራ ባንክ ባለአክሲዮኖቹ፣ ደንበኞቹ፣ ተጠቃሚዎቹና ባለድርሻ አካላት ባንኩ የሚገኝበትን አሁናዊ እውነታ እንዲረዱት ይፈልጋል፡፡ ባንኩ በጠንካራና የተረጋጋ የፋይናንስ አቋም ላይ ሆኖ እየሰራ እንደሆነ፣ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎቹ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መመሪያዎችን መሰረት አድርገዉ እየተፈፀሙ እንደሆነ፣ ከሚዲያ ተቋማትም ጋር ቢሆን በግልጽነትና መርህን ተከትሎ በአግባቡ እየሰራ እንደሆነ እና የባንኩን ባለአክሲዮኖችን፣ ደንበኞቹንና ባለድርሻ አካላትን መብትና ጥቅም ባስከበረ አግባብ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ በድጋሚ ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡
አማራ ባንክ አ.ማ
ከባንክ ባሻገር!
አዲስ አበባ፣ኢትዮጵያ


