የአማራ ባንክ አ.ማ የዳይሬክተሮች ቦርድና የማኔጅመንት አባላት በአማራ ክልል ከሚገኙ የባንኩ ባለድርሻ አካላት እና ከባህር ዳር ዲስትሪክት ሰራተኞች ጋር ከሰሞኑ በባህር ዳር ከተማ የውይይት መድረክ አካሄዱ።
በዚህ የውይይት መድረክ የመንግሥት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች ኃላፊዎችና ተወካዮች እንዲሁም ግለሰቦች ተሳትፈዋል። በመድረኩም የአማራ ባንክ ከምስረታው ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያሳካቸው ዋና ዋና ስኬቶች እና በቀጣይ የሚያከናውናቸው ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች ቀርበዋል።
የአማራ ባንክ ባህር ዳር ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ አሠፋ በዚሁ ወቅት የመነሻ ፅሁፍ በማቅረብ ባንኩ በበርካታ መለኪያዎች አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ገልጸው፣ በፈጣን የዕድገትና የስኬት ጉዞ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በማሳያነትም እ.ኤ.አ በ2025/26 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ድረስ የደንበኞች ቁጥር ወደ 2.8 ሚሊዮን መድረሱን፣ ከታክስ በፊት 1.82 ቢሊየን ትርፍ ማስመዝገቡን፣ የተቀማጭ ገንዘብ ወደ 37.9 ቢሊዮን ብር ማደጉን፣ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን፣ ለደንበኞች የተሰጠ ብድር 33.4 ቢሊዮን ብር መድረሱን እንዲሁም ከ320 በላይ ቅርንጫፎችን በመክፈት ተደራሽነቱን ማስፋቱን ገልጸዋል።
በውይይቱ ወቅት ተሳታፊዎች ባንኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ በግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ንግድ ዘርፎች ያበረከተውን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ አድናቆት ሲገልጹ፣ ባንኩ በክልሉ ተመራጭ የፋይናንስ ተቋም እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል። እንዲሁም ለመንግሥት ሰራተኞች በዝቅተኛ የወለድ መጠን የሚሰጡ የብድር አማራጮች የባንኩን ማህበራዊ ተልዕኮ ለማሳካት አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ተሳታፊዎች በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱ የውይይት መድረክ ባለድርሻ አካላት ስለ ባንኩ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ ከማገዙም በተጨማሪ በባንኩ ላይ የሚሰራጩ የሐሰት መረጃዎችን እና የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን በግልጽ እንዲረዱ አስችሏል ብለዋል።
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንት የደንበኞችን ሀሳብና አስተያየት በማድመጥ እንዲሁም በሥራ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን በመስማት የመፍትሔ አማራጮችን ለማቅረብ የውይይት መድረክ ማዘጋጀታቸው የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀረበው የመነሻ የውይይት ሰነድ መሰረት በመድረኩ የተሳተፉ የተቋማት ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ ባንኩ ከተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ በግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ንግድ ዘርፎች ለመደገፍ ያበረከተው ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ በክልሉ ተመራጭ እንዲሆን እንዳስቻለ ገልጸዋል።
እንዲሁም ለመንግሥት ሰራተኞች በዝቅተኛ የወለድ መጠን የሚቀርቡ የብድር አማራጮች ባንኩ ህብረተሰቡን ለማገልገል የተመሰረተበትን ዓላማ በተግባር እያሳካ መሆኑን በመጠቆም፣ ተግባሩ እንዲቀጥልና እንዲጠናከር አሳስበዋል።
የዳይሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንቱ በበኩላቸው ባንኩ ለቀጣይ 5 ዓመታት የተዘጋጀውን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ወደ ስራ መግባቱን በመግለጽ፣ በዚህም የስራ አፈጻፀምን ማሻሻል፣ የአጋር አካላትን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር፣ ውጤታማነትን ማሳደግ እና የዲጂታል የባንክ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ ላይ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በመጨረሻም እንደዚህ ዓይነቱ የውይይት መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅርብ የስራ ግንኙነት ለመፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሌሎች ከተሞችም ተመሳሳይ መድረኮችን በቀጣይ እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል።
አማራ ባንክ
ከባንክ ባሻገር!
ከባንክ ባሻገር!


