አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፣ ታህሳስ 9 ቀን 2018 ዓ.ም አማራ ባንክ፣ ከወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ጋር ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት በወጋገን ካፒታል ዋና መስሪያ ቤት ተፈራረመ፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የአማራ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) እና የወጋገን ካፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይ. ብሩታዊት ዳዊት ናቸው፡፡
የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የህዝብ አክሲዮን ኩባንያዎች የመመዝገብ ግዴታ ባስቀመጠዉ መመሪያ መሰረት፤ አማራ ባንክ በባለአክሲዮኖቹ የተያዙትን ሰነደመዋለ ነዋዮች በተቀመጠው መስፈርት መሰረት የማስመዝገብ ሂደቱን የደንበኛ ሳቢ መግለጫ (Prospectus) ማዘጋጀትን ጨምሮ እንዲያስተባብርና ሌሎች ከካፒታል ገበያ ጋር የተያያዙ የማማከር ስራዎችን እንዲሰራ ኃላፊነቱ ለወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ በሰጠው መሠረት አማራ ባንክ ለካፒታል ባንኩ አስፈላጊ መረጃዎችን ማቅረብ ችሏል ብለዋል፡፡
አማራ ባንክ የአክሲዮን ገበያ ባልነበረት ጊዜ ከ164,000 በላይ ባለአክሲዮኖችን እምነት በማግኘት የባንኩን አክሲዮኖች ለመሸጥ የቻለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ዘመናዊና የተማከለ የካፒታል ገበያ አማካኝነት የመጡ ተጨማሪ እድሎችንን ለመጠቀምና በኢትዮጵያ እያደገ ባለው የካፒታል ገበያ ውስጥ ባንኩ በሚኖረው ንቁ ተሳትፎ ማለትም በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ላይ የባንኩን አክሲዮኖችን እንዲሸጥ ለማስቻል፣ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ለማቋቋም፣ ተጨማሪ ካፒታል ማሰባሰብ የመሳሰሉ ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሁለቱ ተቋማት የተፈራረሙት ስምምነቶች ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ገልጸዋል።
የወጋገን ካፒታል ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይ. ብሩታዊት ዳዊት በበኩላቸው አማራ ባንክ በአገሪቱ የካፒታል ገበያ ውስጥ ለሚኖረው ሚናና ተሳትፎ ወጋገን ካፒታል ባንክ ላይ ኃላፊነትና እምነት ስለጣለ ያመሰገኑ ሲሆን፣ ኢንቨስትመንት ባንኩ የተሰጡትን ኃለፊነቶች በሚገባ እንደሚወጣ በማረጋገጥ ለአማራ ባንክ የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክተዋል፡፡
አማራ ባንክ
ከባንክ ባሻገር!


