አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ መጋቢት 16 ቀን 2018 ዓ.ም የአማራ ባንክ እና ቪዛ በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ስርዓትን ለማዘመንና ለማሻሻል የሚያስችል ስትራቴጂካዊ አጋርነት መፈፀማቸውን አስታውቀዋል።
ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ ውስጥ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎቶችን ለማሻሻል እና የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት
እንደሚያስችል ተገልጿል።
በስምምነቱ መሠረት፣ አማራ ባንክ የቪዛ ዓለም አቀፍ አውታረ መረብ፣ የደህንነት ደረጃዎችንና ቴክኖሎጂ በመጠቀም የካርድ አገልግሎቱን እንዲያስፋፋ እና የዲጂታል ክፍያ መሠረተ ልማቱን እንዲያበረታ ያግዛል።
በዚህ የአጋርነት ስምምነት መሠረት፣ ባንኩ የቪዛ የቅድመ ክፍያ (Prepaid)፣ የጎልድ እና ፕላቲኒየም ካርዶች እንዲሁም የዴቢት ካርዶችን በማቅረብ ደንበኞች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን የክፍያ ካርዶችን እንዲጠቀሙ ያስችላል። ይህም በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የግብይት ሂደትን በከፍተኛ መጠን ለማሳደግ ይረዳል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ አጋርነቱ የፋይናንስ ስርዓትን ለማጠናከር የሚያግዝ ሲሆን፣ ቪዛ ለአማራ ባንክ ስትራቴጂያዊ ምክር፣ የአደጋ ስጋት፣ የማጭበርበር መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎች እና የፕሮጀክት አመራር ድጋፍ እንዲሁም ከፍተኛ የደህንነት ደረጃዎችን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መፍትሄዎችን ለማቅረብ
ያግዛል።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ባንክ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ እሸቴ የማታ “ይህ ከቪዛ ጋር የተፈጠረው ትብብር ባንካችንን በዲጂታል የታገዘ ባንክ ለማድረግ በምንጓዘው ጉዞ ውስጥ ወሳኝ እርምጃ ነው፤ ደንበኞቻችንን ወደ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ለማስገባት እና የጥሬ
ገንዘብ አልባ ማህበረሰብ ለመገንባት እንደሚያግዝ እንረዳለን” ብለዋል።
በተመሳሳይ፣ የቪዛ የምስራቅ አፍሪካ ኃላፊ
እና የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ እንዳለ በንግግራቸው “ቪዛ በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያዎችን እድገት ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው፤ ከአማራ
ባንክ ጋር ያለው አጋርነት ለደንበኞች የበለጠ ደህንነት ያለውና ቀላል የክፍያ አማራጮችን ለማቅረብ ያግዛል” ብለዋል።
በእለቱ ባንኩ ከቪዛ ጋር ያደረገው ስምምነት ከኢትዮጵያ የብሄራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ጋር የተጣጣመ ሲሆን፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋትና የባንክ አገልግሎትን ለማዘመን ያስችላል። በተጨማሪም በቀጣይ ዘመን 24/7 የክፍያ አገልግሎት ለደንበኞችና ለንግዱ
ማህበረሰብ ለማቅረብ የሚያስችል መሠረት ይፈጥራል።
አማራ
ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ፈጣን እድገት እያሳየ ያለ የፋይናንስ ተቋም ሲሆን፣ ዘመናዊ እና ደንበኛ ተኮር አገልግሎቶችን በማቅረብ ለግለሰቦችና ለንግድ የፋይናንስ አቅምን ለማሳደግ ያለመ ተቋም
ነው።
ቪዛ በዓለም ከ200 በላይ አገራት ውስጥ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት የሚያቀርብ ዓለም አቀፍ መሪ ኩባንያ ሲሆን፣ ተስማሚ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ፈጠራ ያለው የክፍያ መስመር በመጠቀም ኢኮኖሚው እንዲያድግ በመስራት ላይ ያለ ተቋም ነው።



