አዲስ አበባ
አማራ ባንክ በይፋ ከተመሰረተበት ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ባለአክሲዮኖች እምነት፣ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ደንበኞች ድጋፍ፣ በሰራተኞቹ ቁርጠኝነት እና በአገራችን ህዝብ በተሰጠው ከፍተኛ ተስፋ ላይ ተመስርቶ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ አንዱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋም ሆኖ መገንባቱን ቀጥሏል።
የባንካችን እድገት የአንድ ግለሰብ፣ የአንድ ቡድን ወይም የአንድ ውሳኔ ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ በከፍተኛ ህዝባዊ ተሳትፎ እና ትብብር፡ በጋራ ኃላፊነት እና በጠንካራ ተቋማዊ መሠረት የተገነባ በፋይናንስ ዘርፍ በአገር-አቀፍ ብሎም በአለምአቀፍ ብቁ ተወዳዳሪ እና ብራንድ የመሆን ራዕይን ሰንቆ የተመሰረተ ባንክ ነው።
አማራ ባንክ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት፡ የባለአክሲዮኖቹን እምነት፣ የደንበኞቹን ጥቅም እና የተቋሙን ተአማኒነት በማስጠበቅ የባንኩን ሥራ በሕግ፣ በሥርዓት እና በተቋማዊ መርሆዎች መሠረት ለማከናወን ቁርጠኛ መሆኑን ለሁሉም ባለደርሻ አካላት ማረጋገጥ ይወዳል።
የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ራዕይ፡ ተልዕኮ እና ስትራቴጂ በውጤታማነት ሊመሩ የሚችሉ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ልምድ እና እውቀት ያካበቱ የስራ ኃላፊዎችን መመሪያን እና ግልጽ መርህን በተከተለ እና በጠንካራ የውድድር ሂደት (Rigorous Competition Process) በመመልመልና ምርጫ በማካሄድ አደራጅቶ ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይሁን እንጅ ባንኩ ስራውን በተገቢው መንገድ እየሰራ ባለበት ሁኔታ በማህበራዊ ሚዲያ መሰረተ-ቢስ እና ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ በባንኩ አመራር አባላት እና በባንኩ ደንበኞችም ጭምር የሀሰት መረጃ በማሰራጨት መልካም ስምን የሚያጎድፍ እና የባንኩን ገጽታ የሚያጠለሽ እኩይ ተግባር እየተፈፀመ በመሆኑ ባንኩ ለባለአክሲዮኖች፣ ለደንበኞች፣ ለተቆጣጣሪ አካላት፣ ለሰራተኞች እና ለመላው ህዝብ የሚከተለውን ማብራሪያ መስጠት ተገቢ፣ ትክክለኛና አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል።
የአመራር ምልመላ ሂደት እና ተቋማዊ ግልጽነት
ቦርዱ በማንኛውም የተቋም አስተዳደርና የአመራር ሂደት ውስጥ የሃሳብ ልዩነት መኖሩ ተፈጥሯዊ መሆኑን ያምናል። ሆኖም የሃሳብ ልዩነቶች የተቋሙን ህጋዊነት፣ የቦርዱን ስልጣን ወይም የባንኩን ተቋማዊ ጥንካሬ የሚያሳጡ እንዳልሆኑ ለህዝብ ማረጋገጥ ይወዳል።
የባንኩ ከፍተኛ አመራር ምልመላና ምርጫ ሂደት በቦርዱ በፀደቁ የኮርፖሬት ገቨርናንስ መመሪያዎች፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተፈጻሚ በሆኑ መመሪያዎችና መስፈርቶች መሠረት ብሎም በተቋሙ የውስጥ አሠራር ስርዓቶች መሠረት ደረጃ በደረጃ ተከናውኗል። ሂደቱ በብቃት፣ በሙያዊ ብስለት፣ በተገቢ ምዘና እና የአመራር ብቃትን መሰረት ባደረጉ መስፈርቶች ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ በየደረጃው የተሰጡ ውሳኔዎችም በህጋዊና ተቋማዊ ሂደት ተመርተዋል።
በሂደቱ ውስጥ፦
- የቦርዱ ምልመላ፣መረጣና ክፍያ ኮሚቴ በመደበኛ አሰራር ተዋቅሮ ሥራውን አከናውኗል፤
- ለሁሉም የቦርድ አባላት እጩዎችን በተቀመጠው ጊዜ የመጠቆም እኩል ዕድል ተሰጥቷል፤
- የምልመላ እና መረጣ ሂደቱን ዝርዝር ሂደት የሚግልጽ መመሪያ ተዘጋጅቶ ቦርዱ አጽድቋል።
- የተጠቆሙ እጩዎች የትምህርት፣ የሙያ እና የአመራር ብቃት በጸደቀው መመሪያ እና በተዘጋጁ መስፈርቶች መሠረት ተገምግመዋል፤
- ለእጩ ተወዳዳሪዎችን የቅድመ ልየታ (በብሄራዊ ባንክ ዝቅተኛ መስፈርት መሰረት)፣ እንደእየ እጩ ተወዳዳሪዎች መደብ የመወዳደሪያ ስትራቴጅ ዝግጀት፡ የገለጻ፣ የቃለ መጠይቅ እና ለሁሉም እጩ ተውዳዳሪዎች ጥልቅ የሆነ የኋላ ታሪክ ምርመራ (background check) በሚገባ እና በተደራጀ አግባብ ተከናውነዋል፤
- የመጨረሻው ውጤት በተዘጋጁት የምዘና መስፈርቶች መሠረት ተሰርተው የምልመላ እና መረጣ ሂደቱን በግልጽ የሚያሳይ ዝርዝር ሪፖርት ከበርካታ ደጋፊ ሰነዶች ጋር ለዳይሬክተሮች ቦርድ ለውሳኔ ቀርቧዋል፤
የመጨረሻ ውሳኔም በዳይሬክተሮች ቦርድ ሕጋዊ ሥልጣን መሠረት በውይይት እና በድምጽ ብልጫ ውሳኔ በመስጠት ባንኩን በቀጣይ የሚመሩ ከፍተኛ አመራሮችን መርጧል። በመሆኑም የእጩ አመራር ምርጫ ተሳትፎ አጠቃላይ ሂደቶች ላይ ሁሉም የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት በግልፅነት፣ ተጠያቂነትና የኃላፊነት ስሜት በተሞላበት መንገድ ተሳትፏቸውን ያረጋገጡበት ሂደት ተከናውል። ባንኩ በዚህ የከፍተኛ አመራር እጩዎችን የመመልመልና የመምረጥ ሂደት ውስጥ በተቀመጠው የምልመላ እና መረጣ መመሪያ መሰረት የተሰራ መሆኑ ሪፖርት ቀርቦ በቦርድ አባላትም ተረጋግጧል።
አማራ ባንክ ጤናማ የሀሳብ ልዩነት፣ ሙያዊ ክርክር እና በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ውይይትን የሚያከብር ቢሆንም፣ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ያልተረጋገጡ መረጃዎች፣ የተሳሳቱ ትርጓሜዎች ወይም የተቋሙን ስም እና የባንኩ የበላይ ሃላፊዎችን ክብር የሚጎዱ መረጃዎች በሕዝብ ዘንድ መሰራጨታቸው ለተቋሙ እና ለፋይናንስ ዘርፉ አጠቃላይ መረጋጋት የማይጠቅም መሆኑን በፅኑ ያምናል። ይህንን ኃላፊነት የጎደለው ተግባር የሚፈጽሙ አካላት ከዚህ እኩይ ድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል።
ባንኩ በዚህ አጋጣሚ ለባለአክሲዮኖቹ፣ ለደንበኞቹ፣ ለተቆጣጣሪ አካላት፣ ለአጋር ተቋማት እና ለመላው ህዝብ ያለውን ክብር እየገለፀ በየጊዜው ለሚከናወኑ ማንኛውም ተቋማዊ አሰራሮች እና ህጎች እንዲከበሩ ጥብቅ ቁርጠኝነት ያለው መሆኑን በአፅንዖት መግለጽ ይፈልጋል። በቀጣይም ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትን፣ መልካም አስተዳደርን እና ተቋማዊ ጥንካሬን በማስፈን የተጀመረውን የእድገት ጉዞ ለማስቀጠል በሙሉ አቅሙ እንደሚሰራ ያረጋግጣል።
ስለ አማራ ባንክ የወደፊት አቅጣጫ
ባንካችን ትኩረቱን በወጀብ እና በውዝግቦች ላይ ሳይሆን በእድገት፣ በአዳዲስ አገልግሎቶች፣ በዲጂታል ለውጥ፣ በደንበኞች እርካታ እና በአገራዊ ኢኮኖሚ ላይ በሚያበረክተው አስተዋፅኦ ላይ ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል። በከፍተኛ ህዝባዊ ተሳትፎ፡ በባለአክሲዮኖች እምነት፣ በደንበኞች ታማኝነት፣ በሰራተኞች ቁርጠኝነት እና በመንግስት እና በተቆጣጣሪ አካላት ድጋፍ የተገነባው አማራ ባንክ በቀጣይም የእድገት ጉዞውን በጥንካሬ እንደሚቀጥል ባንኩ ሙሉ እምነት አለው። ለዚህ ጉዞው የሚያግዙ ከፍተኛ የባንኩ የማኔጅመንት አባላትን አደራጅቶ የወደፊት ጉዞውን ቀጥሏል።
ለባለአክሲዮኖች፣ ለደንበኞች እና ለህዝብ የቀረበ ጥሪ፣
የአማራ ባንክ ጥንካሬ የሁላችንም የጋራ ጥንካሬ ነው። የባንኩ ስኬት የባለአክሲዮኖች፣ የደንበኞች፣ የሰራተኞች እና የአገራችን ስኬት ነው። ስለሆነም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተረጋገጠ መረጃ ላይ በመመርኮዝ ለተቋሙ ያላቸውን እምነት እና ድጋፍ እንዲቀጥሉ ባንኩ በአክብሮት ይጠይቃል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለያየ መንገድ የባንኩን የውስጥ መረጃዎችን ለሶስተኛ ወገን በተዛባ መልኩ አሳልፈው የሚሰጡ እና የተቋሙን ሚስጥር በማይጠብቁ አንዳንድ የውስጥ አባላት ላይ ባንኩ በማስረጃ በማረጋገጥ የማያዳግም እርምጃ እስከሚወስድ ድረስ በዚህ አጋጣሚ ድርጊታቸው ባንኩን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑና በእውነታ ላይ ያልተመሰረቱ በመሆናቸው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ባንኩ በጥብቅ ያሳስባል።
በተጨማሪም ኃላፊነት በጎደለው እና ተጠያቂነት የሌለ እስኪመስል ድረስ መሰረት-ቢስ በሆነ እና ተቆርቋሪ በመምሰል ግን ከፋፋይ በሆነ መንገድ ባንኩን ብሎም ህዝብን የሚያውኩ የውጭ አካላትም ከዚህ እኩይ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ባንኩ በጽኑ ይመክራል።
ባንካችን በመልካም አስተዳደር፣ በተቋማዊ ጥንካሬ፣ በግልጽነት እና በዘላቂ እድገት ላይ ተመስርቶ የተጀመረውን ጉዞ በወጀብና በውዝግብ ሳይደናቀፍ በተሳካ ሁኔታ እንደሚቀጥል በድጋሚ ያረጋግጣል።
በመጨረሻም ለባንኩ ተቋማዊ ጥንካሬ፣ ለፋይናንስ ሥርዓቱ መረጋጋት እና ለባለድርሻ አካላት የጋራ ጥቅም የሚበጅ ማንኛውም ገንቢ አስተያየት እና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ባንኩ ጥሪውን ያቀርባል።
“ተቋማት በሰዎች ይጀምራሉ፤ በስርዓት ይጸናሉ።”
የአማራ ባንክ!
ከባንክ ባሻገር!


