አማራ ባንክ በጎንደር ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ።

Home / Agreements / አማራ ባንክ በጎንደር ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ።

የአማራ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድና ከፍተኛ አመራሮች በጎንደር ከተማ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሁለት ቀናት የቆየ ውይይት አካሄዱ። ውይይቱ ባንኩ እስካሁን ባስመዘገበው ስኬት፣ የወደፊት ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያተኮረ ነበር።

ውይይቱ ለሁለት የተካሄደ ሲሆን፤ መጋቢት 11 ቀን 2018 ዓ.ም ከጎንደር ከተማ የሁሉም ቅርንጫፎች እና የዲስትሪክቱ ሠራተኞች ጋር ተካሂዷል፤ መጋቢት 12 ቀን 2018 ዓ.ም ደግሞ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ከጎንደር ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተካሂዷል።

በውይይቱ መክፈቻ ላይ የአማራ ባንክ የጎንደር ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዝጋለ ዳኘው የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ ባንኩ ከምስረታው ጀምሮ እስከአሁን ያስመዘገበውን የእድገት ጉዞ እና በ2025/26 በጀት ዓመት የስምንት ወራት አፈጻጸም መሠረት የደንበኞች ቁጥር ወደ 2.8 ሚሊዮን መድረሱን፣ የተቀማጭ ገንዘብ 37.9 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን እና 33.4 ቢሊዮን ብር ብድር ለደንበኞች መሰጠቱን ገልጸዋል። በተጨማሪም ከ320 በላይ ቅርንጫፎችን በመክፈት የአገልግሎቱን ተደራሽነት እያስፋፋ መሆኑን አስታውቀዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የመንግሥት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶችና ግለሰቦች ባንኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ በግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ንግድ ዘርፎች ላይ ያበረከተው ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም ለመንግሥት ሠራተኞች በዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ የሚያቀርበው ባንኩ ሕብረተሰቡን ለማገልገል የተመሠረተበትን ዓላማ እያሳካ መሆኑን ጠቁመው ይህ አይነቱ አገልግሎት እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትና የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች ከባለድርሻ አካላት ጋር በቀጥታ ያደረጉት ውይይት ተሳታፊዎች ስለ ባንኩ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ ከማስቻሉ በተጨማሪ፣ በባንኩ ላይ የሚሰራጭ የሐሰት መረጃና የስም ማጥፋት ዘመቻ በግልጽ እንዲያውቁ እንዳስቻላቸውና ከባንኩ ጋር ያላቸውን ትብብር እንደገና ለማጠናከር የሚያግዝ ውይይት መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይቱ የዳይሬክተሮች ቦርድና የማኔጅመንት አባላት ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚተገበር ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ወደ ተግባር መግባቱን አስታውቀው፣ በዕቅዱ መሠረት የሥራ አፈጻጸምን ማሻሻል፣ የባለድርሻ አካላት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር፣ የገበያ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እና የዲጂታል የባንክ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ማስፋት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በመጨረሻም፣ እንደዚህ ዓይነት ገንቢ የውይይት መድረኮች ባንኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት የሚያስችሉ በመሆናቸው፣ በሌሎች ከተሞችም ተመሳሳይ መድረኮች እንደሚዘጋጁ ተገልጿል።

Download ABa Mobile Banking

Download the app and join our digital world.

Copyright© 2026 Amhara Bank S.C. | All Rights Reserved

wpChatIcon
wpChatIcon