ባንኩ በ2018 በጀት ዓመት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ትርፍ በማስመዝገብ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃር ከ3 እጥፍ በላይ የትርፍ ዕድገት አስመዝግቧል።
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25 ቀን 2018 ዓ.ም
አማራ ባንክ የ2018 በጀት ዓመትን በተቀመጡ የአፈጻጸም መለኪያዎች መሠረት አመርቂ ውጤቶችን በማስመዝገብ በስኬት አጠናቋል። ባንኩ በበጀት ዓመቱ በሃብት አሰባሰብ እና ብድር አቅርቦት፣ በትርፋማነት፣ በተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ በደንበኛ አገልግሎት፣ በዲጂታል ባንኪንግ እና በገበያ ተደራሽነት ጠንካራ እድገቶችን አስመዝግቧል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ትርፍ በማስመዝገብ፣ ከአምናው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ3 እጥፍ በላይ የትርፍ ዕድገት አሳይቷል።
በበርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ ታልፎ የተመዘገበው ይህ ውጤት የባንኩን ጠንካራ የመፈጸም አቅም እና የአደጋ ስጋት አስተዳደር ስራዓት ብሎም የቦርዱን፣ የአመራሩን እና ሰራተኛውን አይበርገሬነት፣ ትጋት እና ቁርጠኝነት ያሳየ ሆኗል።
ባንኩ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በመላ ሀገሪቱ ከ321 በላይ ቅርንጫፎችን በመክፈት እና ከ3 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት የፋይናንስ ተደራሽነቱን በማሳደግ በዘርፉ ተወዳዳሪ መሆን ችሏል።
ይህ ውጤት የተገኘው መላው የአማራ ባንክ ሰራተኞች ባሳዩት ትጋት፣ ቁርጠኝነት እና የቡድን ጥረት ነው። በተጨማሪም የባንኩ ማኔጅመንት በሰጠው ውጤታማ አመራር፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ ባደረገው ቀጣይነት ያለው ክትትል እና ስትራቴጂካዊ ድጋፍ የተገኘ መሆኑን ባንኩ ይገልጻል። አማራ ባንክ ለዚህ ታላቅ ስኬት ዋነኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት መላው ሰራተኞቹ ከልብ የመነጨ ምስጋናና ከፍተኛ እውቅና ያቀርባል።
አማራ ባንክ ባጋጠሙት ተግዳሮቶች ሁሉ ከጎኑ ለቆሙ፣ እምነታቸውን ለጣሉበት፣ ለውጤቱ የጋራ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ክቡራን ደንበኞቹ፣ ባለአክሲዮኖቹ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ ተቆጣጣሪ ተቋማት፣ የንግድ አጋሮቹ እና ለመላው ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ምስጋናውን ያቀርባል። የተገኘው ስኬት የጋራ ጥረት ፍሬ መሆኑን ባንኩ በጽኑ ያምናል።
በመሆኑም ባንኩ ለመላው ሰራተኞቹ፣ ለዳይሬክተሮች ቦርድ፣ ለማኔጅመንቱ፣ ለባለአክሲዮኖቹ፣ ለደንበኞቹ እና ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ለተገኘው አመርቂ ስኬት እንኳን ደስ አላችሁ እያለ አዲሱ የ2019 በጀት ዓመትም የፋይናንስ አቅሙን ይበልጥ በማሳደግ ለባለድርሻ አካላቱ የላቀ እሴት ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ያረጋግጣል።
አማራ ባንክ
ከባንክ ባሻገር!


